Thursday, June 25, 2015

የአየር ሀይል ሃላፊዎች በዘረኝነትና በሙስና ተዘፍቀዋል ተባለ


ኢሳት ዜና (ሰኔ 18፥ 2007)
በኢትዮጵያ አየር ሀይል ውስጥ ባለው ዘረኝነትና አስተዳደራዊ በደል በመንገፍገፍ ከሰራቱ የሚለዩት የበረራ ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መገኘቱን እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋቱን የአየር ሀይል ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።  በህገ-ወጥ የሰው ዘውውር የአየር ሀይል አባላት የታሰሩ መሆናቸውንም  ለመረዳት ተችሏል።
በ2007 አ/ም ብቻ አስር የበረራ ባለሙያዎች ስርአቱን በመክዳትና ወደ እስር ቤት በመጋዝ ከአየር ሀይሉ የተለዩ ሲሆን ፤ በአየር ሀይሉ ውስጥ የሰፈነው የአንድ ብሄር የበላይነት ወደ መንደር እየወረደ ስለመሆኑም በአስረጂነት ይጠቅሳሉ። የምስራቅ አየር ምድብ ሙሉ በሙሉ በበላይነት የሚቆጣጠሩት የትግራይ ክልል ውቅሮ ተወላጆች እንደሆኑ ተጠቅሷል።
የአየር ምድብ አዛዥ ኮሎኔል አበበ ተካ፣ የዘመቻ መኮንን ኮሎኔል ሙሉ ገብሬ፣ የዊንግ አዛዥ ሻለቃ ጸጋኣብ ካሳ፣ የስኳድሮን አዛዥ መቶ አለቃ አማኑኤል ወ/ገብርኤል ሁሉም የውቅሮ ተወላጆች መሆናቸን ከአየር ሃይል ምንጭ መረዳት ተችሏል። በማእከላዊ ሆነ በአየር ምድብ ከምእራብ አየር ምድብ ውጭ በሁሉም የሃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙት የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ ወደታች ወደ መንደር እየተሳሳሳቡ መሆኑንም ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ ከአየር ምድብ አዛዦች ብቸኛ የሌላ ብሄር ተወላጅ የምእራብ አየር ምድብ አዛዥ ኮሎኔል ይልማ መርዳሳ ብቻ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
በሙስና ረገድም ያለጠያቂ በዘረፋ ውስጥ የተዘፈቁት የህወሃት ታጋይ የነበሩ መሆናቸው የተገለጽ ሲሆን፣ በ 2006 አም SF-260 የተባለ የመለማመጃ አውሮፕላን ጥገና ተብሎ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የወጣ ሲሆን፣ ጥገናው የተካሄደበት በሃገር ቤት ባለሙያና ቁሳቁስ ቢሆንም በዘረፋው የተጠረጠሩት አልተጠየቁም።
በተመሳሳይም በቀድሞ አየር ሃይል ኣዛዥ ሜጀር ጄነራል ሞላ ሃይለማሪያም ትእዛዝ በ 20 ሚሊዮን ብር መለዋወጫ እንዲገዛ ተወስኖ፣ በሳምንት ጊዜ ውስጥ በኪሳራ ተመልሶ እንዲሸጥ ሲደረግ የጠየቀ ሰው አልነበረም።
በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ በሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉት የህወሃት ታጋዮች፣ የመንግስት ሄሊኮፕተሮችን ሴቶችን ለማዝናናት እንደሚጠቀሙበትና፣ አብራሪዎችም ለዚህ ተግባት ተመድበው ሲሰሩ መቆየታቸውን የአየር ሃይል ምንጮቻችን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት ግንቦት ሰባትን ልትቀላቀሉ ስትሉ ተደርሶባችኋል በሚል ከታሰሩት አብራሪዎች አንዱ፣ የአንድን ባለስልጣን ወዳጅ ከደብረዘይት ወደባህርዳር፣ ከባህርዳር ወደአዋሳ እንደሚያመላልስ ለ10 ቀን ግዳጅ ተሰጥቶት ይህንኑ ሲፈጽም መቆየቱን ምንጮች ያስታውሳሉ። የትራስፖርት ሄሊኮፕተር በተለይ ወደሶማሊያ ሄደው ሲመለሱ የኮንትሮባንድ እቃ ጭነው የሚመለሱ ሲሆን፣ ንብረትነቱ የበረራ ሃላፊዎች ይሆናል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል በላስልጣኖች ኮንትሮባንድን ጨምሮ በልዩ ልዩ ሕገወጥ ተግባሮች በሙስና ሲዘፈቁ፣ በተዋረድ ያለ ግለሰብም በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ድርጊት ተሳታፊ በመሆን፣ እንደአቅማቸው ገንዘብ እንደሚያሰባስቡ ለኢሳት የደረሰው ማስረጃ ያስረዳል።
በዚህ ድርጊት ተዋናይ ናቸው የተባሉ መቶ አለቃ ዳንኤል ገ/መድህን፣ መቶ አለቃ ተክሌ አብርሃ የተባሉ የህወሃት አባላት፣ ከደላሎቹ ጋር የታሰሩ ቢሆንም፣ በኮሎኔል አበበ ተካ ጣልቃ-ገብነት ሁለቱ በነጻ ሲለቀቁ  ደላላው 20 ኣመት ተፈርዶበታል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከ ምርጫ 1997 ወዲህ ከ 30 የሚበልጡ አብራሪዎች የከዱት ሲሆን፣ በ 2007 አም ብቻ ከስርአቱ የተለዩትና የታሰሩት ደግሞ 10 ያህል መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፈው ታህሳስ  MI-35 ሄሊኮፕተር ይዘው ሁለት አብራሪዎችና አንድ ቴክኒሺያን መክዳታቸው ይታወቃል።
ሌሎች አምስት አብራሪዎች ማለትም መ/አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ መ/አለቃ ዳንኤል ግርማ፣  መ/አለቃ ብሩህ አጥናዬ፣   መ/አለቃ አንተነህ ታደመ ደግሞ ስርኣቱን ከድታችሁ ግንቦት ሰባትን ልትቀላቀሉ ኣስባችኋል በሚል ታስረዋል።

No comments:

Post a Comment