Sunday, May 10, 2015

ይድረስ ለእናቴ ከ አሌክስ አብርሃም


በዚች ምድር ላይ የእኔን ደብዳቤ ከሰማይና ምድር በላይ አግዝፋ የምትመለከት …ቃሌን እንደንጉስ ቃል በፍርሃት ሳይሆን በፍቅር ተንሰፍስፋ የምትሰማ …ጓጉታ የምታደምጥ…ቃሌ የሰፈረበትን ወረቀት ባጠቡኝ ጡቶቿ … በልጅነት እንቅልፍ በናወዝኩበት ደረቷ ላይ ለጥፋ ላገኘችው ሁሉ በደስታ እየተፍለቀለቀች ‹‹ልጀ ደብዳቤ ፃፈ ›› እያለች የምታውጅ ፍጥረት ብትኖር አንች እናቴ ብቻ ነሽና ይሄንን ደብዳቤ ፃፍኩልሽ …
‹‹ለጤናየ ደህና ነኝ ›› ስልሽ እንባ የኳተሩ አይኖችሽን ወደሰማይ ቀና አድርገሽ ፈጣሪሽን ስለእኔ ደህንነት እልፍ ጊዜ የምታመሰግኝ ሰው አንች ብቻ ነሽና ህመሜ ህመምሽ ለሆነው እናቴ… ጤናየም ጤና እንዲሆንልሽ በጣም ጤና ነኝ ! ‹‹ብታይ አምሮብኛል ›› ስልሽ ፊትሽ እንደሙሴ ቆዳ በደስታ እንደሚያበራ አውቃለሁ …በኑሮ ውጣ ውረድ ፊትሽ ላይ የተጋደሙ መስመሮች ውብ የአበባ መስኖዎች መስለው በመሃላቸው ሃሴት እንደሚፈስ አውቃለሁና አዎ እማማ አምሮብኛል!በጣም ደህና ነኝ !!
‹‹አንች ግን ደህና ነሽ ?›› አልልም!! ሁልጊዜም ህመምሽን አፍነሽ ብሶትና ናፍቆትሽን በእንባሽ መቀነት ቋጥረሽ መልስሽ ‹‹ደህና ነኝ ..እኔ ምናለብኝ ›› ነውና ፈጣሪ እንደአፍሽ እንደእኔም ምኞት ደህና እንዲያደርግልኝ በየቀኑ በየሰአቱ እጠይቀዋለሁ ! እማማ እሳሳልሻሁ …አንገት ለአንገት ተናንቄ ሰዓቶችን ባቆማቸው ቀናቶችን እንደጨው አምድ ባሉበት ብገትራቸው ደስታየ ነው ….ለእኔኮ አይደለም ….አንች እንዳታረጅብኝ …የእርጅና ጨካኝ እጆች ሲያደክሙሽ እንዳላይ …የሞት ጥላ በላይሽ እንዳያንዣብብ !!…
አንችኮ በምድር ላይ በፍፁም ልብ የመወደድ አንድ እድሌ እኮነሽ … በምድር ላይ ዘላለማዊ የእንክብካቤ እቅፍ ውስጥ የምኖርበት እጣ ፋንታየ ነሽ …ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ነጭ ፀጉር ፀጉሮችሽ መሃል ስመለከት ትንፋሽ አጠረኝ … ፀጋ ነው እርጅና ይሉኛል …ለእኔ ግን እንደዛ አይሰማኝም እፈራለሁ ….ፀጋየ ሳቅሽ ነው …ፀጋየ ከቤት ደጅ ወዲያ ወዲህ ስትይ የማይደክም ትጋትሽን መመልከት ነው !!
ባለፈው ደግሞ መንገድ ላይ ያለፍሽኝ ቀን እየሳኩ ሳቅፍሽ ምን አልሽኝ ‹‹እርጅና መጣ ይሄው ልጀን እንኳን ማለፍ ጀመርኩ›› እማማ በምድር ላይ ምንም ነገር ቢያልፈኝ ያን ያህል አላዝንም …እርጅናን አልፈራውም ሞት የጥፍር ቁራጭ ያህል በእኔ ላይ ፍርሃት አይጭርም …ግን ለእኔ ለራሴ ሲሆን ብቻ ነው …ላንች ግን . . .
መፅሃፍ ቅዱስ ሳነብ ‹‹ዘላለማዊ ህይዎት›› መኖሩን ሲያበስረኝ በደስታ እቦርቃለሁ … አሁንም ላንች !!…ዘላለም ሳታረጅ ዘላለም ሳትደክሚ ዘላለም በህይዎት የምትኖሪበት ዘላለም መኖሩ ልቤን በሃሴት ይሞለዋል …እናም ከዚህኛው አለም የእድሜ አጥር ጭንቀቴ ትንሽ እረጋጋለሁ … ዘላለማዊነት ለሁሉም እናቶች እላለሁ !
ፈጣሪ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለውን ፍቅር የእናቶች ትከሻ እንዲችለው አድርጎ መፍጠሩ ሲገርመኝ ይኖራል …የትም አደጋ ቢፈጠር ደውለሽ ‹‹ደህና ነህ ›› ስትይኝ ይገርመኛል … በድፍን ኢትዮጲያ የምኖረው እኔ ብቻ በድፍን አለም የምኖረው እኔ ብቻ የሆንኩ ይመስል አፍጋኒስታን ቦንብ ሲፈነዳ አዲስ አበባ ያለሁ እኔ ላይ ፍንጣሪው አለመድረሱን ከፍንጣሪው ፍጥነት ቀድመሽ የምትጠይቂ ደህንነቴንም ከራሴ ደጋግመሽ ካልሰማሽ የማታምኝ …ምርጥ ፍጥረት እማማ!! አንችን ሳስብ …ፈገግታየ ውስጥ ሃዘን ሃዘኔ ውስጥ ፈገግታ አለ! እወድሻለሁ…አከብርሻለሁ ….ለአንች የሚሆን ስጦታ በምድር ላይ የለም ! ሁልጊዜ እንደምትይው ‹‹የእኔ ስጦታ የአንተ ደህና መሆን ነው ›› ትይ የለ ….እና ራሴን የምጠብቀው ለዛ ነው !
አዎ… ስጋየ የስጋሽ ቁራጭ ነውና የማይረባ ቦታ አውየ ላረክሰው አልሻም …እራሴን ስጠብቅ አንችን እንደጠበኩሽ ይሰማኛል ….‹‹ማንስ ምን አገባው ›› የሚል ትእቢት ከአፌ አይወጣም ! ሁሌም በሁሉም ነገሬ አንች ያገባሻል …እግዚአብሔር ሃዘንን ይያዝልሽ እኔ ግን ሃዘን የሚፈጥርብሽን ነገር ሁሉ ከእኔ ላርቅ ሁልጊዜም ፍላጎቴ ላይ እንደዘመትኩ ነው … የአለም እናቶች ሁሉ …ከቁሳቁስ በላይ ከገንዘብ በላይ ከልጆቻቸውም ስኬት በላይ የልጆቻቸውን ደህንነት ያሳስባቸዋልና …ወጣቱን የከበበው አሰቃቂ ሱስ ፣ በሽታና ሌላም ጣጣ ሁሉ የእናቶች አንገት ላይ ያረፈ ስለት እንደሆነ አውቃለሁ ! ስለዚህ ልብሽን ከሚሰብር ነገር ሁሉ ራሴን ከመጠበቅ በላይ ጠንካራ ስጦታ የለም !
እማማ አባባን ደግሞ ሰላም በይልኝ …እና ደግሞ የዛሬውን የእናቶች ቀን ተገን አድርጌ ከልቤ እንዳመሰገንኩት ንገሪልኝ ….አንተ አንዲትን ሴት በምድር ላይ ካለው ታላቅ ስልጣንና ከፍታ ሁሉ በላይ ወደሆነው የእናትነት መዓረግ ከፍ ያደረክ ጨዋ ደግና ጥሩ ሰው ነህ በይልኝ ! አለም የሚዘክረውን አንድ ቀን ዘላለማዊ ያደረክ እናቴን በየቀኑ የተንከባከብክ ያከበርክና እኔን ልጅህንም ዘውድ አድርገህ በእናቴ እራስ ላይ ያኖርክ ምርጥ አባት ነህ ብሎሃል በይልኝ ! ሁለታችሁንም ረዥም እድሜ ….በማምሻዋ እንደምትፍለቀለቅ ጀምበርም ውብ የደስታ ብርሃን በወላጅነት አድማሳችሁ ላይ የሚፍለቀለቅበት ህይዎት ይስጣችሁ …እወዳችኋለሁ አከብራችኋለሁ !!
ልጃችሁ!!
መልካም የእናቶች ቀን !!

No comments:

Post a Comment