Sunday, March 20, 2016

Ethiopians in Norwey protested against Deportation of political asylum seekers

ኖርዌይ ኢትዮጵያውያን የፓለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው ለመመሰስ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረገችውን ስምምነት የሚቃወም ታላቅ ሰልፍ በታላላቅ የኖርዌይ ከተሞች ተካሄደ!!

ኢትዮጵያውያን በስደት ከሚኖሩባቸው የተለያዩ የአውሮፓና ስካንዴኔቪያን ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኖርዌይ ስትሆን በኖርዌይ ሃገር ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባል ኢትዮጵያውያን የፓለቲካ ስደተኞች ይገኛሉ። እነዚህ ስደተኞች ከሌላው ሀገር ለየት የሚያደርግ ጠንካራ የፓለቲካ አቋም ያላቸው መሆኑም ይታወቃል። ስደተኞቹ በተለያየ ጊዜያት የገዢውን ፓርቲ ብልሹ አስተዳደር የሚያጋልጡ የፓለቲካ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ሆኖም ግን የኖርዌ መንግስት እ.ኤ.አ በ2012 ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በኖርዌይ የሚኖሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስገድዶ ወደ ሃገር ለመመለስ የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። ሆኖም ግን ይህ ስምምነት በተለያዩ ምክንያቶች ተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል። ኖርዌይ በድጋሚ አሁን በያዝነው አመት በፌብርዋሪ ወር እንደገና ስደተኞችን አስገድዶ ወደ ሀገር የመመለሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴዎድሮስ አደሃኖም ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በኖርዌይ የሚገኙ ታላላቅ የዜና አውታሮች ሰሞኑን ሲዘግቡ ሰንብተዋል።
ይህንኑ ስምምነት አስመልክቶ በኖርዌይ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማህበር ስምምነቱ ትክክል እንዳልሆነ ተቃውሞውን ለመግለፅ በማርች 15፣ 2016 ሰልፍ አዘጋጅቶ ነበር። ይህ የተቃውሞ ሰልፍ በሶስት ታላላቅ የኖርዌይ ከተሞች፦ በኦስሎ፤ በበርገን እና እስታቫንገር ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በታላቅ ተቃውሞ ተካሂዷል። ስደተኞቹ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተለይ በቅርቡ በሀገራችን በአደባባይ እየተገደሉ ያሉ ወገኖቻችንን የያዙ ምስሎችንና የኖርዌይ ዜግነት ያላቸውና ከደቡብ ሱዳን ታፍነው በኢትዮጵያ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉንት የአቶ ኦኬሎ አኳይ ፎቶግራፍ እንዲሁም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ፎቶግራፎች በመያዝ ስለነሱም አያይዞ ለኖርዌይ ፓርላማ ተወካይ ጥያቄ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ እየታወቀ ሰዎች በየሰከንዱ እየተገደሉ ባለበት ወቅት ሀገሪቱ በብዙ አቅጣጫ የህዝብ አመፅ ባለበትና ገዢው ፓርቲም ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ሰዎችን እየገደለና እያሰረ ባለበት ጊዜ ስደተኞችን አስገድዶ ለመመሰል ስምምነት ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ፤ እንዲሁም የኖርዌይ መንግስት ለኖርዌጅያን ዜጎች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች መዘዋወር አደገኛ መሆኑን መግለጫ እየሰጠ ባለበት ሁኔታ የፓለቲካ ስደተኞችን አሳልፎ መስጠት ሰብአዊነት የጎደለውና የስደተኛ መብት ህግን የሚጥስ መሆኑን ኢትዮጵያውያኑ በሰልፉ ላይ ተናግረዋል።
በሰልፉ ላይ ከተለያዩ ድርጅቶች የተወከሉ ተወካዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን በኖርዌ የስደተኛ መብት ተከራካሪ የሆኑ የኖርዌጅያን ድርጅቶችም በሰልፉ ላይ ተገኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚያውቁና ስምምነቱንም እንደማይደግፉ አቋማቸውን ገልፀዋል። በመጨረሻም የስደተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር የስደተኛውን የአቋም መግለጫ በማንበብ ሰልፉ በተያዘለት ሰአት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
ኢትጵያ ለዘላለም ትኑር
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌ!!

No comments:

Post a Comment