ኢሳት (ጥር 20 2008)
አለም አቀፍ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ የሰጠው ምላሽ ከሚጠበቀው በታችና አስከፊ መሆኑ አንድ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋም አርብ አስታወቀ።
በቀጣዩ ወር ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች 500 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ካልተቻለም በርካታ ሰዎች ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ የህጻናት አድን ድርጅቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በሃገሪቱ ታሪክም ሆነ በሌሎች ሃገራት ካሉት ጋር ሲነጻጸር አስከፊ ቢሆንም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በቂ ትኩረትን አልሰጠም ሲሉ በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናትን አድን ድርጅት ተወካይ ሚስተር ጆን ግራም ማስታወቃቸውን ኢዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት በ1977 ተከስቶ ከነበረው የረሃብ አደጋ ጋር ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱን ሃላፊው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ግብረ ሰናይ ተቋማት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይኸው በስድስት ክልሎች ጉዳትን ኣያደረሰ ያለው ድርቅ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ በሰው ህይወት ላይ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።
በተለይ በድርቁ ምክንያት የዘር እህላቸው ያለቀባቸው አርሶ አደሮች ለቀጣዩ የእርሻ ወቅት የሚዘሩት እህል የሌላቸው በመሆኑ ችግሩ አስከፊ እየሆነ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
በሃገሪቱ ያለው የእርዳታ መጠንም ተረጂዎችን ለቀጣዩ ወራቶች ለማቆየት የማይበቃ መሆኑንና ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ድርጅቱ ገልጿል።
በቅርቡ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሃገሪቱ ለሶስት ወር የሚበቃ የእህል ክምችት አላት ሲሉ ከሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መሃገራቸው ይታወሳል።
ቃል አቀባዩ ይህንን ቢሉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎችን ለሁለት ወር ያህል እንኳን ለማቆይየት አስቸጋሪ መሆኑን በድጋሚ ይፋ አድርጓል።
Source : Esat
No comments:
Post a Comment