ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስትና አለማቀፍ ድርጅቶች በሰጡት መረጃ መሰረት የተረጂው ጠቅላላ ቁጥር 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ደርሷል፡፡ መረጃዎች ግን ከዚህ በላይ መሆኑን ያመለክታሉ።
የተጠቀሰው አሃዝ ቀደም ሲል በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው የሚረዱ ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኢትዮጵያዊን ወገኖችን ይጨምራል ተብሎአል። ይሁን እንጅ መንግስት ያዘጋጀው እና አለማቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የሚጠቅሱት ሰነድ በምግብ ለስራ የታቀፉ ዜጎች ቁጥር 3 ሚሊዮን 800 ሺ ሳይሆን 8 ሚሊዮን ነው። በዚህም መሰረት የእለት ደራሽ እርዳታ የሚፈልገው ህዝብ ቁጥር እስከ 13 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል። አሃዙ በከተሞች የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎችን አይጨምርም።
ከብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ላቀረበው የዕርዳታ ጥያቄ የእንግሊዝ መንግስት 45 ሚሊዮን ፓውንድ ለመለገስ ቃል የገባ ሲሆን አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ጃፓን ምላሽ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን አረጋግጠዋል ብሏል፡፡ መንግስት 4 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጿል።
መንግስት 222 ሺህ 639 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ ሀገር ፣ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን በቆሎ ከሀገር ውስጥ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑንና ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮ ወደተረጂዎቹ እንደሚደርስ ገልጿል፡፡
በቅርቡም የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በ11 ከተሞች ለሚገኙ 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ 10 ቢሊየን ብር በጀት መያዙን መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የተረጂው ወገን ቁጥር እያሻቀበ መምጣት ያሳሰበው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ፣ ቀድሞ በግብርና ሚኒስቴር ስር አንድ መምሪያ የነበረውን የአደጋ መከላከል ራሱን ወደቻለ ባለለስጣን አሳድጎታል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት( ዩኤስ አይ ዲ) በድረገጹ ባሰፈረው መረጃ እድሜያቸው ከ 5 አመት በታች ከሆኑት ህጻነት መካከል 44 በመቶው በከፍተኛ የምግብ እጥረትና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይሰቃያሉ። ከእነዚህ መካከል 28 በመቶው ከአማካኝ ክብደት በታች ናቸው። 31 ሚሊዮን 600 ሺ ህዝብ ደግሞ ለሰውነት የሚያስፈልገውን በቂ ምግብ አያገኘም።
ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ላለፉት 11 አመታት ማግኘቱን የሚገልጸው መንግስት፣ በአንድ የዝናብ ወቅት የተፈጠረውን የምግብ እጥረት በራሱ ለመቋቋም አለመቻሉ፣ በኢኮኖሚ እድገቱ ጥንካሬ ላይ ጥያቄ እያስነሳ ነው።
አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና አለማቀፍ ድርጅቶች ለሚቀጥሉት 3 ወራት 598 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ እንደያስፍልግ ገልጸዋል። 258 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ቢሆንም፣ ቀሪው ገንዘብ አሁንም እየተጠበቀ ነው።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment