Sunday, October 4, 2015

መለስ ዜናዊ አቡነ አረጋዊ ሆነ እንዴ? – ከተማ ዋቅጅራ



Meles Zenawi - Satenaw
ቤተ ክርስትያን የራሷ የሆነ ህግ ያላት በዶግማ እና በቀኖና የተመሰረተች የማትለወጥ፣ የማትሻሻል፣ በምድር የምትኖር ሰማያዊት አገር፣ በምር ያለች የሰማዩን ምስጥር የምታመሰጥር፣ በምድር እያለች በሰማይ ያለውን እግዚአብሔር የምትሰብክ፣ የእግዚአብሔር ቤት፣ የሰላም መገኛ፣ የህይወት ምንጭ የሆነች መንፈሳዊ ቤት ናት። የቤተክርስትያን ተልዕኮዋ ምድራዊ መንግስትን መስበክ ሳይሆን ሰማያዊ መንግስትን መስበክ ነው። ቤተ ክርስትያን ለምድራዊ ገዢ መበርከስ ሳይሆን ለሰማያዊው አምላክ መንበርከክ ነው። ለርካሽ ፖለቲካ ማከናወኛ ተብሎ በዚህች የእግዚአብሔር ቤት በተባለች፣ የሰማይ ደጅ የተባለች፣ የገሃነብ ደጆች አይችሏትም የተባለችውን ቤተክርስትያን ላይ የግለሰብ ፎቶ ከሃይማኖት አባቶች ጋር አጸዷ ላይ መስቀል በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። በማን አለብኝነት ይሄንን ስህተት የሰሩ አካላት ንስሃ ካልገቡ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈርድባቸው እና የሚያስኮንናቸው ትልቅ ኃጥያት ነውና በቤተክርስትያን ላይ እጃችሁን የምታስገቡ የፖለቲካ አካሎች እንዲሁም ግልገሎጬን ጠብቁ፣ በጎቼን ጠብቁ፣ ጠቦቶቼን ጠብቁ፣ ተብሎ የሃዋርያትን ስልጣነ ክህነት የተቀበላችሁ አባቶች ካህናት ለርካሽ ፖለቲካ ማከናወኛ የሰማያዊውን ቤት፣ የሰላም ሰገነት፣ የፍቅር አምድ፣ የህይወት መሰረት፣ የነጻነት አርማ፣ የዘላለም ቤት በሆነችውን በቤተክርስትያን የማይገባ ስራ መስራት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቃችሁን ስራ በድፍረት ከመስራት እንድትቆጠቡ ያስፈልጋል።
ቤተክርስትያን ቅዱሳን ሰዎችን አክብራ ስራቸውን፣ ተጋድሎአቸውን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን የጽድቅ አክሊል እንደየክብራቸው በስዕል በመግለጽ ገድላቸውን በመጻፍና በማስተማር ክብራቸውን የምታከብር ናት። ቤተክርስትያን ቅዱሳንን ቅዱስ የሚለውን ስም የምትሰጣቸው በስጋዊ ህይወታቸው ዘመን እግዚአብሔርን በማምለክ የጸሎት ብርታታቸውን በማየት፣ አጋንንትን ድል የሚነሱበትን የእምነታቸውን ጽናት በመመልከት፣ በህይወታቸው ጭምር ወንጌልን በመስበክ ያላመኑትን ወደ እምነት መመለስ፣ እግዚአብሔርን የማያውቁትን ህዝብ እግዚአብሔርን በማሳወቅ፣ የራቁትን በማቅረብ፣ የቀረቡትን በማጽናት፣ ነገስታትን ሳይፈሩ ሃያላንም ሳያፍሩ እውነትን በማስተማር፣ ፍቅርን በመስበክ፣ አንድነትን በማጽናት፣ የእግዚአብሔ ፍቅር እንዲኖረን፣ የህዝብ አንድነት እንዲሰፍን፣ እርስ በራስ መዋደድን በህዝብ እንዲሰፍን በማድረግ፣ ባልንጀራን እንደራስ አድርጎ መውደድን በመመስከር፣ ክርስቶስ የጠሉትን አፍቅሮ የገደሉትን አድኖ የሰደቡትን አስተምሮ ወደ ፍቅሩ ጠርቶ ልጆቹ እንዳደረገ ሁሉ ቅዱሳኑም ከክርስቶስ የተማሩትን እንዲሁ በማድረግ በፍቅር ኖረው ፍቅርን ሰብከው ስለፍቅር መስክረው በህይወታቸው ጭምር ለክርስትና መስክር ያለፉትን ቤተክርስትያን ገድላቸውን ጽፋ ስዕሎቻቸውን ስላ ምዕመኗን ስታስተምር ኖራለች ወደፊትም ትኖራለች።
ታዲያ መለስ ዜናዊን ቤተክርስትያን በር ላይ መስቀላቸው ምን ማለታቸው ነው? ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና ነገሩ የቤተክርስትያን አባቶች ልታስቡበት ይገባል። የመለሰ ዜናዊን ምስል ቤተክርስትያን ለይ ለመስቀል የተነሳሳችሁ ግለሰቦች ምን ነክቷችሁ ነው? ቤተክርስትያን እና መልስ አይተዋወቁም። ቤተክርስትያን ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት የምታስተምር አስተምራም መንግስተ ሰማያት የምታወርስ ቤት ናት። መለስ ግን ስለ አንድ ብሔር ታላቅነት የሚናገር፣ በኢትዮጵያኑ መሃል ፍቅር ያጠፋ፣ አንዱ ከሌላው በጠላትነት እንዲተያዩ ያደረገ፣ ጊዜአዊ መንግስቱን ለማጽናት ሚሊዮኖችን የገደለ፣ ያስገደለ፣ ወንጀል ቤቱ የሆነ፣ ጥፋት ህይወቱ የሆነ፣ ማጋጨት ባህሪው የሆነ፣ ሚሊዮኖችን ያስለቀሰ፣ ሚሊዮኖችን የበደለ፣ ሚሊዮኖችን በጠላትነት እንዲተያዩ ያደረገ፣ የፍቅርና የሰላም ቤት ቋንቋዋ ፍቅር ብቻ በሆነ ቤተክርስትያን ላይ መለጠፍ ምን ማለት ነው?። አሰቦት ገዳምን የደፈረ፣ ዋልድባን ያስቆፈረ፣ ጳጳስን በጋርድ ያስጠበቀ፣ ኸረ ለየትኛው ስራው ነው ቤተክርስትያን ላይ ሊያሰቅለው የቻለው?። ለርካሽ ፖለቲካ ማሳኪያ ብላችሁ የሰማይ ደጅ የሆነችውን ቤተክርስትያን አታቆሽሹ። ለጊዜአዊ የስልጣን ጥቅም ብላችሁ ዘላለማዊ የሆነችውን ቤት አታርክሱ።
በቅድስናቸው ቤተክርስትያን ያገለገሉ፣በህይወታቸው ክርስቶስን የመሰሉ፣ በአንደበታቸው ውሸት ያልተናገሩ፣ መለያየትን እና ጥላቻን ያላስተማሩ፣ በፍቅር ኖረው ፍቅርን አስተምረው፣ የእጃቸው በረከት ለታመሙት ፈውስ የሆኑት እነዚህ ናቸው በቤተክርስትያ ውስጥም ውጪም ስዕላቸው የሚሰቀለው። እንደነዚህ ያሉት የቤተክርስትያን ከዋክብቶች ናቸውና። ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ቤተክርስትያን የማትቀበለውን ስራ በመስራት ቤተክርስትያንን እና ህዝቦቻን የሚያስቆጣ ነውና ነውር የሆነ ያልተማረ ስዕል በመለጠፍ አይን ያወጣ ስህተት እንዳያደርጉ ከወዲሁ ልንናገር ያስፈልጋል። የቤተክርስትያንን ህግ ለቤተክርስትያን ተዉላት። ቤተክርስትያን በምድር ሆና የሰማዩን መንገድ የምታስተምር እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤት ናትና።
ይቆየን
ከተማ ዋቅጅራ
04.10.2015
Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment