Sunday, June 28, 2015

ሚድሮክ ወርቅ በሁለት አመታት ብቻ ከ429 ሚሊዮን ብር በላይ አልከፈለም ተባለ


ሰኔ ፲፰ (አስራ ሰምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በመጥቀስ ሪፖርተር እንደዘገበው በማዕድን ሚኒስቴር ላይ በ2006 ዓ.ም. አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ላይ ባደረገው የክዋኔ ኦዲት አገሪቱ ከፍተኛ ገንዘብ ማጣቷን አረጋግጧል፡፡
የማዕድን ሥራ አዋጅ ቁጥር 678/2002 የከበሩ ማዕድናት ላይ ስምንት በመቶ ፣ያልከበሩ ማዕድናት ላይ ደግሞ ስድስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ መጣሉን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
“ማዕድን ሚኒስቴር ከሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ላይ አምስት በመቶ ብቻ ሮያሊቲ ክፍያ በመሰብሰቡ፣ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 በጀት ዓመት ከሚድሮክ የወርቅ ሽያጭ መንግሥት ሊያገኝ የሚችለውን 252.9 ሚሊዮን ብር ማጣቱን፣ እንዲሁም ካልከበሩ ማዕድናት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብቻ 413 ሺ 394 ብር ማጣቱን፣ በድምሩ በሁለት ዓመታት ውስጥ 253.37 ሚሊዮን ብር የሮያሊቲ ገንዘብ አለመሰብሰቡን” ጋዜጣው ዘግቧል።
ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2000 ዓ.ም. ማምረት የጀመረ ቢሆንም፣ ማዕድን ሚኒስቴር ተቋሙን በየወቅቱ እየተከታተለ ሒሳቡን እንዳልመረመረ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
መንግሥት በሚድሮክ የወርቅ ማዕድን አክሲዮን ማኅበር ላይ ያለውን የነፃ ድርሻ በሕግ አግባብ ማስላት ባለመቻሉ፣ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ 108.7 ሚሊዮን ብር እንዲሁም እስከ መጋቢት 2006 ዓ.ም. ድረስ 67.4 ሚሊዮን ብር በድምሩ 176.2 ሚሊዮን ብር አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን ገንዘብ አለማግኘቱዋን ጋዜጣው ዘግቧል።
ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች እንደሚሉት የሼክ ሙሃመድ አላሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ወርቅ በ1990 ዓም የቀደሞውን አዶላ ወረቅ ማውጫ በርካሽ ዋጋ ከመንግስት በፕራይቬታይዜሽን ስም ከገዛበት ጊዜ ጀምሮ የሮያለቲ ክፍያ መክፈል ቢጠበቅብትም ለረጅም ጊዜ ሳይከፍል ቆይቷል። ድርጅቱ የትርፍ ምርት ግብር የሚባለውን ክፍያ ዘግይቶ መክፈል መጀመሩን የሚያስታውሱት ምንጮች፣ የፌደራሉ ዋና ኦዲተር ከ2 ሺ አመት ምህረት ጀምሮ ምርመራ ማካሄዱ በቂ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። ድርጅቱ ከ1990 እስከ 2000 ዓም ያልከፈለው የሮያሊቲ ክፍያ እንዲሁም በእነዚህ አመታት ውስጥ ያስገባው ገቢና ትርፍ ተመዝኖ ኦዲት ሊደረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ ። ይህንኑ ጉዳይ ለመንግስት ያሳወቁ የቀድሞው የማእድን ሚኒስቴር የመምሪያ ሃላፊ ከስራ እንዲባረሩ ተደርጓል።

No comments:

Post a Comment