Friday, May 29, 2015

በምርጫ ቦርድ ውጤት የኢህአዴግ ደጋፊዎች ለሁለት ተከፍለዋል


ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ የግንቦት15ቱን ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉ ከተገለጸ በሁዋላ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሁለት ተከፍለዋል። ምንጮች እንደገለጹት በርካታ ፊደል ቀመስ አባሎቹ ኢህአዴግ አሸነፍኩ
ያለበትን የድምጽ ልዩነት አልተቀበሉትም። ውጤቱን የሚቃወሙ የግንባሩ አባላት ” ህዝቡ ከእንግዲህ በሰላም መንግስት እቀይራለሁ የሚለው እምነቱ ተሟጦ የሃይል አማራጭን ብቻ እንዲመለከት ከማድረጉም በላይ፣ የሃይል አማራጭን
የሚከተሉ ሃይሎች በህዝቡም ሆነ በአለማቀፉ ማህበረሰብም የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል” በማለት ለድርጅቱ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ተገኘ የተባለውን ውጤት ከመደገፍ አልፈው፣ ህዝቡ እንዴት ለተቃዋሚዎች ይህን ያክል ድምጽ ሊሰጥ ቻለ በማለት በቁጭት አስተያየት የሚሰጡ ደጋፊዎች መኖራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
ኢህአዴግ እያሰባሰበ ባለው መረጃ ላይ እንደተገለጸው፣ አንዳንዶች ” ይህ ህዝብ ምን አይነት ልቡ የማይታወቅ ከሃዲ ህዝብ ነው! እንዴት ይሄን ሁሉ ልማት እያዬ ለተቃዋሚ ድምጹን ሊሰጥ ቻለ?” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ቦርድ ራሱ ባወጣው ሰሌዳ መሰረት የምርጫውን ውጤት መግለጽ የነበረበት ግንቦት21 ቢሆንም፣ የግንቦት20 በአልን ለማድመቅ እንዲረዳ በሚል ከእቅዱ በፊት እንዲገለጽ መደረጉን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ
ዘጋቢያችን ገልጿል።
ኢህአዴግ በየክልሉ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የፌሽታ በዓላትን አዘጋጅቷል። ትናንት የገዢው ፓርቲ ደጋፊ አርቲስቶች ያዘጋጁት የኪነጥበብ ምሽት በብሔራዉ ቲያትር ተካሂዷል፡፡፡ በርካታ የፌዴራል የመንግስት መ/ቤቶች በተለያዩ ሆቴሎች
በዓሉን ለማክበር ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግን አሸናፊነት ቢያውጅም መድረክ የተባለው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የምርጫውን ውጤት አልተቀበለውም። ድርጅቱ ምርጫው አነስተኛ የሚባሉ መስፈርቶችን እንኳ ያላሟላ በማለት አጣጥሎታል። መድረክ
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ገለልተኛ የሚባሉ ሰዎች ተመርጠው መምርራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫውን በተመለከተ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ያለው ነገር የለም። መንግስት የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎችን እያዋከበ በማሰር ላይ መሆኑ፣ ፓርቲውን አጣብቂኝ ውስጥ ሳይከተው አልቀረም። ሰማያዊ የምርጫውን
ውጤት ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም።
የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን በተመለከተ በርካታ እጸጾችን አውጥተው ቢገልጹም፣ ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደማያቋርጡ አስታውቀዋል። የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ ዲፕሎማቶች
በምርጫ ታዛቢነት እንዳይሰታፉ መከልከላቸው፣ ምርጫው አሳታፊ አለመሆኑንና የተለያዩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መታሰራቸውን በመግለጫቸው አመልክተዋል።
በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ በርካታ አስገራሚ ክስተቶች ለኢሳት እየደረሱ ነው። ግንቦት12 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ ልዩ ቦታው ላንቻ ወይም ጠመንጃ ያዥ ነዋሪ የሆነ አንድ የ12 ዓመት ህፃን የኢህአዴግን የምርጫ መልዕክት ያየዘ
ፖስተር ከተለጠፈበት ግድግዳ ላይ ቀደሃል በሚል 6 ወር ተፈርዶበታል።
በአዲስ አበባ ችሎት በሚባል ቦታ አርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ሁለት ማየት የተሳናቸው ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ወጣቶቹ የተያዙት አንደኛው ሙሉ ሰማያዊ ልብስ ለብሶ በመውጣቱ በተፈጠረው አተካራ ነው። የአካባቢው
ሴት ካድሬ አንደኛውን ማየት የተሳነው ወጣት “ለምን ሰማያዊ ልብስ ለበስክ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነሆይ?” በማለት ጥያቄ ስታቀርበለት፣ ጓደኛው “ምን አገባሽ ምንስ ብለብስ!” የሚል መልስ መስጠቱን ተከትሎ፣ ግለሰቧ በብስጪት
ለደህንነቶች ባስተላለፈችው ጥቆማ መሰረት ሁለቱም ወጣቶች በድንገት ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ ታስረው ይገኛሉ።
መነን መሰናዶና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ፀሃይ ጮራ ት/ቤት ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው 20 መምህራንና 30 ተማሪዎች የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲ አባላት ናቸው በሚል ዝርዝራቸው ለጸጥታ አካላት ተልዕኮ በልዩ ሁኔታ ክትትል እንዲደረግባቸው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከምርጫ በፊት ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment